Comboni

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ቴክኖሎጂ ሁሉንም ሰው ሊጠቅም እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሚያዝያ ወር እንዲሆን ያዘጋጁትን የጸሎት ሐሳብ ይፋ አድርገዋል። በዓለም አቀፉ የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ በኩል ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክታቸው ቴክኖሎጂ ሁሉንም ሰው በተለይም እጅግ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ሊያገለግል እንደሚገባ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን – ቫቲካን

አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እና አጠቃቀማቸውን በማስመልከት ባቀረቡት ሃሳብ፥ ቴክኖሎጂ የሰውን የእርስ በርስ ግንኙነትን መተካት እንደማይችል፣ ሰብዓዊ ክብርን ሊያስጠብቅ እንደሚችል እና የዘመናችንን ችግሮች መጋፈጥ እንዲችሉ ለማድረግ እንደሚችሉ ተስፋ መኖሩን በወርሃዊ የጸሎት ሃሳባቸው ገልጸዋል።

በማኅበራዊአውታረመረቦችዓለምውስጥ

ዓለም በማኅበራዊ ሚዲያ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመጣው የሰው ሠራሽ የማሰብ ችሎታ በተጥለቀለቀበት ጊዜ “ቴክኖሎጂ እግዚአብሔር የሰጠን የማሰብ ችሎታ ፍሬ ነው” ሲሉ አጽንዖት ሰጥተው፥ ሆኖም ግን አላግባብ መጠቀም አሉታዊ ውጤቶችን ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

ቴክኖሎጂዎች መገለልን ሊያስከትሉ እንደሚችል እና በቴክኖሎጂ አማካይነት እውነተኛ የእርስ በርስ  ግንኙነት ማድረግ እንደማይቻል ገልጸው፥ ከሰዎች ጋር ፊት ለፊት ሳይሆን ነገር ግን በስልካችን ላይ ብዙ ጊዜን የምናሳልፍ ከሆነ ችግር ሊያስከት እንደሚችል አስረድተዋል።

“በተለያየ መንገድ እየጨመረ የመጣው የ “ስክሪን” አጠቃቀም ከጀርባው የሚናገሩ፣ የሚስቁ እና የሚያለቅሱ እውነተኛ ሰዎች መኖራቸውን እንድንረሳ ያደርገናል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። በዚህም የ “ሳይበር” ላይ ጥቃት እና ጥላቻ በማኅበራዊ ሚዲያ አውታረ መረቦች ላይ መስፋፋት እንደሚጀምር ተናግረዋል። ቴክኖሎጂ ጥሩ ቢሆንም ሌሎችን ሳያካትት ለጥቂቶች ብቻ ጥቅም የሚሰጥ ከሆነ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ፣ የሥራ ዕድል፣ የትምህርት እና ሌሎች የእኩልነት ማጣቶችን እንደሚያስከትል አስረድተዋል።

ቴክኖሎጂበሰውልጅአገልግሎት

እነዚህን አደጋዎች ለማስወገድ ሁሉም ሰው ቴክኖሎጂን በአገልግሎት ላይ እንዲያውሉት ያበረታቱት ቅዱስነታቸው፥ ቴክኖሎጂ ሰዎችን ለማስተባበር፣ የተቸገሩትን ለመርዳት፣ የሕሙማንን ሕይወት ለማሻሻል፣ የግንኙነት ባህልን ለማዳበር እና የጋራ መኖሪያ ምድራችንን ከውድመት ለመጠበቅ እንደሚያግዝም ተናግረዋል።

ቴክኖሎጂ የተፈጠረው የሰውን ልጅ ከእውነታ እና ከተጨባጭ ግንኙነት ለማራቅ እንዳልሆነ አስረድተው፥ በመሆኑም ሁሉም ሰዎች በእጅ ስልክ ላይ የሚያጠፋውን ረጅም ጊዜ በመገደብ እርስ በርስ በአካል መገናኘት እንደሚገባ አሳስበዋል። “ዋናው ጉዳይ ቴክኖሎጂን ከግንኙነት ጋር በማመጣጠን እያንዳንዳችን ወንድማማቾች፣ እህትማማቾች እና የአንድ አባት ልጆች መሆናችንን እንድንገነዘብ ማስቻሉን ማወቅ ነው” ብለዋል።

Scroll to Top